ጌቴሴማኒ

March 30, 2015

ጌቴሴማኒ የአትክልት ምድር፣
እማኝ አድርጌ ልጥራሽ ምስክር፣
አድምጠሻልና የሰውን ልጅ ጽዋ ጣር።
የአባቱን ፊት ሲሻ፣
ሊሞላለት የፍቃዱን ድርሻ፣
ሲጨክን ሊሸከም መስቀሉን፣
ታዝበሻልና መራራ ትግሉን።
ጌቴሴማኒ ንገሪኝ የሰዓቲቱን ጭንቅ፣
የሰው ልጅ ኃጢያት ሆኖ ሊደቅቅ፣
የመስቀሉን ጽዋ ሊጨልጥ ሲማቅቅ።
ንገሪኝ እሲቲ ጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ፣
የመታዘዙን ሚስጢር በፈቃዱ የመግባቱን መላ፣
የኃጢያትን ጽዋ ሲጨልጥ መከራ፣
ስራውን ሊፈጽም የሕይወቱን እንጀራ፣
መንፈስ ተዘጋጅታ ስጋ በደከመበት ስፍራ።
የደሙን ነጠብጣብ ላብ ጠጥተሻልና፣
ታዝበሻልና የመራሩን ጽዋ ፈተና፣
የቆረጠበቱን ሊያቀና ጎልጎታ፣
ካራው ወደ ሚያርፍበቱ ቦታ።
በሰው ቦታ ገብቶ ለመስቀል ሞት ታዞ ሊቀጣ፣
ልጆችን ሊወልድ ሲያምጥ የጽድቅን ፍሬ ሊያወጣ፣
ወልድ ሲጨክን በኃጢያት ፍርድ ሊመታ፣
ደሙ ካፈርሽ ሲዋሃድ ታዝበሻል ጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ።
ጌቴሴማኒ የአትክልት ምድር፣
እማኝ አድርጌ ልጥራሽ ምስክር፣
አድምጠሻልና የሰውን ልጅ ጽዋ ጣር።

Please reload

Recent Posts

March 20, 2020

Please reload

Archive