ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ —ፈቃድ (ክፍል አስር)

November 11, 2017

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ... እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን...” (ሉቃ. 11፡1-2)

ጌታ ባስተማረው ጸሎት ውስጥ የምንጸልየው ሌላው ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ ነው። ብዙ ጊዜ አንደሚባለው ጸሎት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምናስቀይርበት ሳይሆን እኛ የእርሱን ፍቃድ አውቀን ወደ ፈቃዱ የምንገባበት ነው። በሰማይ የእግዚአብሔር ፈቃድ በፍጹም ትከናወናለች። በምድር ፈቃዱ ትፈጸም ዘንድ ግን የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ያስፈጋል።

የእግዚአብሔር ሰው ዶክተር ማይልስ ሞንሮ ሲናገር “ጸሎት እግዚአብሔር በምድር እንዲሰራ የምንፈቅድበት መንገድ” ነው ብሏል። ለዚህ ምክንያቱ እግዚአብሔር በቃሉ ምድርን የመግዛትን ስልጣን የሰጠው ለሰው ስለሆነ ነው። (ዘፍ. 1፡27) ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር ቃሉን የሚሽር (የሚጻረር) አምላክ ስላልሆነ ለሰው በሰጠው የማስተዳደር ስልጣን ያለ ሰው ፍቃድ አይገባም። ስለሆነም የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር እንዲሆን ስንጠይቅ እርሱ በማንኛውም ጉዳያችን ጣልቃ ገብቶ ፍጹም የሆነው ፈቃዱ ይከናወን ዘንድ ነው። ስለዚህ ነው እግዚአብሔር ምድርን በተመለከተ ከፍተኛ ስልጣን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው። እናስታውስ፦ ቃሉ እንደሚለን በምድር የምናስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምንፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። (ማቴ. 18፡18) ነገር ግን በምድር የእግዚአብሔር ፈቃድ ይከናወን ዘንድ ማለትም በምድር የምናስረው በሰማይ የታሰረውን፤ እንዲሁም በምድር የምንፈታው በሰማይ የተፈታውን እንዲሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅና መፈለግ አለብን።

ቃሉ እንደሚያስተምረን የእግዚአብሔር ፍቃድ በጎ፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም ነው። (ሮሜ. 12፡2) የእግዚአብሔር ፍቃድ መልካም ነው። በፈቃዳችን ለፍቃዱ ስናድር በጎነቱ በሕይወታችን ይገለጣል። እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈቃዱ ስንጨክን ለጊዜው ምንም እንኳ ጽዋው መራራ ቢሆንም በፈቃዱ በሄድነው መስመር መጨረሻ በጎነቱ ታገኘናለች። ለኛ ደስታችን ያለው በፍቃዱ ውስጥ ነው። በእርግጥ አለ እግዚአብሔር ፍቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ የለም። ፈቃዱ ፍጹም ነው። የእግዚአብሔር ፍቃድ በሕይወታችን ሲከናወን ያን ግዜ ለተፈጠርንበት አላማ እየኖርን ነው።

ወገኖቼ፦ እግዚአብሔር ለኛ መልካም ነው። ለኛ ያለው ሃሳብ በጎ ነው። ለኛ ያለው ሃሳብ ፍጻሜና ተስፋ ያለው ነው። ፍቃዱን መፈለግና በፍቃዱ ውስጥ መግባት ትልቅ በረከት ነው። አባታችን ሆይ ፍቃድህ በሕይወታችን ትሁን። አሜን! 

Please reload

Recent Posts

March 20, 2020

Please reload

Archive